Thursday, 28 January 2016

ተውሂድ የነብያት ሁሉ ጥሪ!


التوحيد دعوة الرسل
ተውሂድ
የነብያት ሁሉ ጥሪ!

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ በጣም አዛኝ በሆነው

              ይህንን መልዕክት ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ለማስተላለፍ ለረዳን አላህ ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ የአላህ ሰላትና ሰላም በመልዕክተኛው በቤተሰቦቻቸው እና በባልደረቦቻቸው ላይ ይሁን፡፡
አላህ እንዲህ ይላል ፡-

الْيَوْمَ أَكْمَلْتُ لَكُمْ دِينَكُمْ وَأَتْمَمْتُ عَلَيْكُمْ نِعْمَتِي وَرَضِيتُ لَكُمُ الْإِسْلَامَ دِينًا [٥:٣]

(ዛሬ ሀይማኖቻችሁን ሞላሁላችሁ፡፡ ፀጋዬንም በእናንተ ላይ ፈፀምኩ፡፡ ኢስላምንም ከሀይማኖት በኩል ለእናንተ ወደድኩ) አል ማዒዳህ 3

በዚህ አንቀጽ እንደተገለፀው የአላህ ዲን ሙሉ በሆነ መልኩ በመልዕክተኛው አማካኝነት ተላልፏል፡፡ ለኛ የሚበጅ ነገር ሆኖ ሳይጠቁሙን ያለፉት ነገር የለም፡፡   
ከዓብዲላህ ኢብን ዓምር ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ የተከበሩት የአላህ መልዕክተኛ (ﷺ)  እንዲህ ይላሉ፡-

‹‹ለህዝቦቹ የሚያውቀውን መልካም ነገር መጠቆምና ከሚያውቅላቸው ክፉ ነገር ማስጠንቀቅ ግዴታ ቢሆንበት አንጂ ከእኔ በፊት (አንድም) ነቢይ አልነበረም›› ፡፡ 

ነብያት ይዘዋቸዉ ከመጡት መልዕክቶች ተቀዳሚ አጀንዳ አድርገዉ ያብራሩት በአላህ አንድነት ማመንና ብቸኛ ተመላኪነቱን ማረጋገጥ ተውሂድን ነዉ፡፡ ይህ የነብያት ፈለግ ነዉ፡፡ይህ ፈለጋቸዉ የሙስሊሞችን የዳእዋ አካሄድ የሚቀርፅ ነዉ፡፡ ትክክለኛ ዳዕዋ በዋነኝነት ከሚንቀሳቀስባቸው መሰረታዊ ነጥቦች መካከል ዋነኞቹ በተውሂድ በሱናና በዒልም የታነፀ ማህበረሰብ ማፍራት ነዉ፡፡

     እያንዳንዱ ሙስሊም ሊያውቃቸው የሚገቡ መሰረታዊ ቁርዓናዊና ሀዲሳዊ ትምህርቶችን በተከበሩት በመልዕክተኛው ባልደረቦች(ሰሀቦች) ግንዛቤ መረዳት ይገባዋል፡፡

F አላህ እኛን የፈጠረን በእርሱ ላይ ማንንም ሳናጋራ ልናመልከው ነው፡፡ ይህንንም ቀጥሎ ያለው አንቀፅ ይጠቁመናል፡፡

((وَمَا خَلَقْتُ الْجِنَّ وَالْإِنسَ إِلَّا لِيَعْبُدُونِ))    الذاريات: ٥٦

(ጋኔንንም ይሁን ሰውን ሊያመልኩኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም) አልዛሪያት 56

የአላህም መልዕክተኛ (ﷺ)  ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ ይህንኑ እዉነታ እንዲህ በማለት ይገልፁታል

((አላህ በባሮቹ ላይ ያለው መብት እርሱን ሊያመልኩት ከእርሱም ጋር ማንንም ላያጋሩ ነው፡፡))