Wednesday, 16 December 2015

ከቀብር ጋር ተያያዥነት ያላቸው ክልክል ተግባሮች

ከቀብር ጋር ተያያዥነት ያላቸው ክልክል ተግባሮች

የእስልምና የመጀመሪያዎቹ ዘመናት ላይ ቀብርን መጐብኘት ተከልከሎ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከድንቁርና ህይወት በመላቀቅ እንግዳ ስለነበሩና የተውሂድን ወሰን ለመጠበቅ ሲባል ነበር:: ሰዎች እምነታቸውን ሲያሳምሩ ከፍተኛ ስፍራ ሲሰጡት፣ ማስረጃዎቹ ግልፅ ሆነው ልቦች ውስጥ ሲሰርፅና የሽርክ ውዥንብሮች ሲጋለፁ ቀብርን መጐብኘት ዓላማው ተገድቦ ተፈቀደ፡፡

ቡረይዳ ኢብን ሁሰይብ እንዳስተላለፉት የአላህ መልዕክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለምእንዲህ ብለዋል
‹‹ከዚህ በፊት ቀብርን እንዳትጐበኙ ከልክያችሁ ነበር አሁን ግን ጎብኙ፡፡››

አቡሑረይራ እንዳስተላለፉት ነብዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለምእንዲህ ብለዋል    
                   
 ‹‹ቀብርን ጐብኙ ሞትን ያስታውሳችኋል፡፡››

    አቡ ሰዒድ አል ኹድሪይ እንዳስተላለፉትም የአላህ መልዕክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለምእንዲህ ብለዋል
‹‹ቀብርን መጐብኘት ከልክያችሁ ነበር አሁን ግን ጐብኙ ትምህርት ይሰጣችኃል፡››
                                           
  አነስ ኢብኑ ማሊክም እንዳስተላለፉት የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ብለዋል

 ‹‹ቀብርን መጐብኘት ከልክያችሁ ነበር አሁን ግን ጐብኙ ምክንያቱም ልብን ያርሳል፣ አይንን ያነባል፣ አኺራን ያስታውሳል፡፡ ነገር ግን የተከለከለን ቃል እንዳትጠቀሙ፡፡››

 ቡረይዳህ እንዳስተላለፉት የአላህ መልዕክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂወሰለም ቀብር ሲጐበኝ እንዲህ እንዲባል አስተምረዋል፦
 "السلام عليكم أهل الديار من المؤمنين والمسلمين وإنا إن شاء الله بكم لاحقون أسأل الله لنا ولكم العافية"

አሰላሙ ዓለይኩም አሕለ ዲያር ሚነል ሙእሚኒነ ወልሙስሊሚን ወኢና ኢንሻ አላሁ ቢኩም ላሂቁን አስአሉ ላሐ ለና ወለኩሙል ዓፊያ

ትርጉሙ፦

 (የአካባቢው ምእመናንና ሙስሊም ህዝቦች ሆይሰላም በእናንተ ላይ ይስፈን እኛም በአላህ ፈቃድ ተከታዮቻችሁ ነን፡፡ አላህ እኛንም እናንተንም እንዲጠብቅ እለምናለው፡፡”      

እነዚህና መሰል ሀዲሶች እንደሚጠቁሙት ቀብርን መጐብኘት ክልከላው ተነስቶ ለሁለት ታላላቅ ዓላማዎች ሲባል እንደተፈቀደ ነው፡፡

አንደኛ፡አኺራን፣ ሞትንና ማለቅን በማስታወስ ዱንያን ችላ ለማለት እንዲሁም በቀብር ሰዎች ትምህርት በመውሰድ እምነትን ለማጠናከርና ከአላህ ጋር ያለንን ግንኙነት በማሳመር ቸልተኝነትን ለማስወገድ፡፡፡

 ሁለተኛ፡ለሙታኖች አላህ በማዘን ኃጢኣታቸውን እንዲምርና ይቅር እንዲላቸው በመለመን መልካምን መዋል፡፡ከላይ ያሳለፍናቸው ማስረጃዎች የሚጠቁሟቸው ሲሆኑ ከነዚህ ሌላ ከቀብር የሚገኝ ነገር እንዳለ የሚሞግት ማስረጃ ይጠበቅበታል፡፡ 

በሌላ በኩል ከቀብርና ከጉብኝቱ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ነገሮችን ሐዲስ ለተውሂድ ድንበር ጥበቃ ሲል ከልክሏል  እነዚህን ማንኛውም ሙስሊም ከጥመት ለመጠበቅ ሲል ሊያውቃቸው ይገባል፡፡

ድግምት

           1. ድግምት፦

 ሲህር” (ድግምት) በዓረብኛ ቋንቋ ስውር የሆነና ምክንያቱ ያልታወቀ ነገር ማለት ነው፡፡

         ሸሪዓዊ ትርጉሙ፦

 ልብን ወይም አካልን በማሳመም ወይም በመግደል ተፅዕኖ የሚያሳድር እንዲሁም በባልና ሚስት መካከል የሚለያይ ልፍለፋና ትብተባ ሲሆን ነገር ግን ሁሉም ተፅዕኖ ሊያደርግ የሚችለው በአላህ ፍቃድ ብቻ ነው:: ድግምት ኩፍር ሲሆን ድግምተኛም በአላህ የካደ ካፊር በመሆኑ አኺራ ላይ ምንም ዕጣ ፈንታ የለውም፡፡

 አላህ እንዲህ ይላል፦

 ‹‹ሰይጣናትም በሱለይማን (ሰሎሞን) ዘመነ መንግስት የሚያነቡትን (ድግምት) ተከተሉ፡፡ ሱለይማንም አልካደም፤ (ድግምተኛ አልነበረም) ግን ሰይጣናት ሰዎችን ድግምትን የሚያስተምሩ ሲኾኑ ካዱ፡፡ ያንንም በባቢል በሁለቱ መላእክት በሃሩትና ማሩት ላይ የተወረደውን ነገር (ያስተምሩዋቸዋል)፡፡ «እኛ መፈተኛ ነንና አትካድ» እስከሚሉም ድረስ አንድንም አያስተምሩም፡፡ ከእነሱም በሰውየውና በሚስቱ መካከል በርሱ የሚለዩበትን ነገር ይማራሉ፡፡ እነርሱም በአላህ ፈቃድ ካልኾነ በርሱ አንድንም ጎጂዎች አይደሉም፡፡ የሚጎዳቸውንና የማይጠቅማቸውንም ይማራሉ፡፡ የገዛውም ሰው ለርሱ በመጨረሻይቱ አገር ምንም እድል የሌለው መኾኑን በእርግጥ ዐወቁ፡፡ ነፍሶቻቸውንም በርሱ የሸጡበት ዋጋ ከፋ! የሚያውቁ በኾኑ ኖሮ (ባልሠሩት ነበር)፡፡››

(አል በቀራህ 12)

 በተቋጠሩ ክሮች ላይም መትፋት አንዱ የድግምት ክፍል ነው::  አላህ እንዲህ ይላል፦

 በል «በተፈልቃቂው ጎህ ጌታ እጠበቃለሁ፡፡ ከፈጠረው ፍጡር ሁሉ ክፋት፡፡ ከሌሊትም ክፋት ባጨለመ ጊዜ፤በተቋጠሩ (ክሮች) ላይ ተፊዎች ከኾኑት (ደጋሚ) ሴቶችም ክፋት፡፡ከምቀኛም ክፋት በተመቀኘ ጊዜ፤ (እጠበቃለሁ በል)፡፡»

(አል ፈለቅ 1-5)


 ከተንኮለኛና ምቀኞች ሁሉ አላህ ይጠብቀን!!!