Wednesday, 16 December 2015

ዓቂዳ ማለት ምን ማለት ነው?

ዓቂዳ በዐረብኛ ቋንቋ “አሰረ ፣ አጠበቀ ፣ ቋጠረ…” ከሚሉ ጥሬ ቃላት የተገኘ ነው፡፡ የስርወ ቃል ትርጉሙም በኃይል አጥብቆ መቋጠርን ያመለክታል፡፡ የአብዛኛዎቹ ኡለማዎች (ኢስጢላሀዊ) የስስምነት ፍቺ በአማኙ ዘንድ ፍፁም ጥርጣሬ የሌለበት ቁርጥ ያለ እምነት (ኢማን) ማለት ነው፡፡

      ኢስላማዊ አቂዳ አላህ (ሱብሀነሁ ወተዓላ) በጌትነቱ፣ በአምለክነት፣ በስሞቹና በባህሪያቱ ብቸኛ መሆኑን ይገልፃል፡፡ አቂዳ የሆነው ኢማን በአላህ፣ በመላእክቱ፣ በመጻህፍቱ፣ በመልዕክተኞች፣ በመጨረሻው ቀንና በቀደር (ክፉም ሆነ ደጉ በአላህ ቅድመ ውሳኔ መሆኑን) ማመን ነው፡፡

      ከዚህም በተጨማሪ በተረጋገጠ መልኩ በተላለፉት የዲን መሰረቶችና መርሆዎች፣ ከህዋሳት ንግዛቤ በራቁ (የገይብ) ጉዳዮች ማመንን ይጨምራል፡፡ እንዲሁም በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወርቃማ የእስልምና ክፍለ ዘመናት በሕይወት ኖረው ያለፉ የቀናው ጐዳና የሃይማኖት መሪዎች የደረሱበትን ስምምነት (ኢጅማዕ) መቀበል ነው፡፡ በአጠቃላይ ለአላህ ትዕዛዛት፣ ፍርድና መልዕክተኛውን በመከተል ረገድ ያለአንዳች ማመንታት እጅ መስጠትና በቁርጠኛነት ማመን ማለት ነው፡፡
      ከዚህ አጠቃላይ ግንዛቤ በመነሳት ኢስላማዊ አቂዳ አላህ (ሱብሀነሁ ወተዓላ)  ለባሪዎቹ ለመረጠው፣ የወደደውና የሰጠው ብቸኛ እምነት መሆኑን ማወቅና በፍፁም ልብ መቀበል ይገባል፡፡ ይህም ሲባል በእነዚያ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወርቃማ የእስልምና ክፍለ ዘመናት የኖሩት ሰሀባዎች እና ታዕቢዮች የተጓዙበትን ቅን የእምነት ጐዳና የተከተሉ የሐቀኛ ምህመናን የአሕሉ ሱና ወልጀመዓ እምነት ነው፡፡


      ከዚህ በተጨማሪም ኢስላማዊ አቂዳ ሌሎች እሱን የሚያመለክቱና የሚተኩት ተላዋጭ መጠሪያዎች አሉት፡፡ እነርሱም አተውሂድ፣ አሱንና፣ ኡስሉዲን፣ አልፊቁሀል አክበር፣ አሸሪዓ እና አል ኢማን በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡

No comments:

Post a Comment