የሽርክ መፈጠር ምክንያት፦
ለመጀመሪያ ጊዜ የሰው ልጆች ውስጥ ሽርክ የተፈፀመበት ምክንያት ደጋግ ባሮችን በማወደስና በማሞካሸት ወሰንን በመተላለፍ ነበር፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
ﻭَﻗَﺎﻟُﻮﺍ ﻟَﺎ ﺗَﺬَﺭُﻥَّ ﺁﻟِﻬَﺘَﻜُﻢْ ﻭَﻟَﺎ ﺗَﺬَﺭُﻥَّ ﻭَﺩًّﺍ ﻭَﻟَﺎ ﺳُﻮَﺍﻋًﺎ ﻭَﻟَﺎ ﻳَﻐُﻮﺙَ ﻭَﻳَﻌُﻮﻕَ ﻭَﻧَﺴْﺮًﺍ ٧١: ٢٣ ]
ﻭَﻗَﺪْ ﺃَﺿَﻠُّﻮﺍ ﻛَﺜِﻴﺮًﺍ ﻭَﻟَﺎ ﺗَﺰِﺩِ ﺍﻟﻈَّﺎﻟِﻤِﻴﻦَ ﺇِﻟَّﺎ ﺿَﻠَﺎﻟًﺎ[ ٧١: ٢٤ ]
አሉም «አምላኮቻችሁን አትተዉ፡፡ ወድንም፣ ሱዋዕንም፣ የጉሥንም፣ የዑቅንም ነስርንም አትተው፡፡ በእርግጥም ብዙዎችን አሳሳቱ፡፡ ከሓዲዎችንም ጥመትን እንጅ ሌላን አትጨምርላቸው» (አለ)፡፡ [ኑህ 23-24]
እነዚህ በኑህ ዘመን የነበሩ የመልካም ሰዎች ስሞች ነበሩ፡፡ ሲሞቱ ለማስታወስ እንዳይረሱ በምስላለቸው ሀውልቶች ተገንብቶላቸው በስሞቻቸው ተሰየሙ፡፡ የዚህ ተግባር መጨረሻ ግን እነርሱን ማምለክ ሆነ፡፡
ይህን ታሪክ ኢብኑ ዐባስ እንዲህ እንዲህ በማለት ይተርካሉ
‹‹የኑህ ህዝቦች ውስጥ የነበሩ ጣዖታት ከጊዜ በኋላ ወደ ዓረብ ምድር ገቡ፡፡
“ወድ” ደውመተል ጀንደል ውስጥ ላሉ ለከልብ ጐሳዎች፣
“ሱዋዕ ” ለሑዘይል ጐሳ፣
“የጉስ ” መጀመሪያ ለሙራድ ጐሳ: ከዚያ ለበኒ ጉጠይፍ ፣
“የዑቅ” ለሑምዳንና “ነስር” ደግሞ ለዚል ኪላዐህ ቤተሰቦች ለሂምየር ሆኑ፡፡
እነዚህ የኑህ ህዝቦች ውስጥ የነበሩ የመልካም ሰዎች ስም ነበሩ፡፡ እነዚህ ሲሞቱ ሸይጧን ለህዝቦቻቸው በቦታቸው ላይ ሀውልት እንዲተከልና በስሞቻቸው እንዲሰየሙ በመከራቸው መሰረት ፈፀሙት ከተገነቡ በኋላ ግን ለተወሰኑ ጊዜያቶች አይመለኩም ነበር፡፡ ነገር ግን የታሪኩ እውቀት ሲወገድ ይመለኩ ጀመር፡፡›› [ቡኻሪ ዘግበውታል]
ኢብኑ ጀሪር አጠበሪም ሙሀመድ ኢብን ቀይስን ጠቅሰው በዚህ አንቀፅ ዙሪያ እንዲህ ይላሉ፡-
‹‹አሉም «አምላኮቻችሁን አትተዉ፡፡ ››
‹‹እነዚህ ሰዎች ደጋግ ባሮች ስለነበሩ ሰዎች አርዐያ ያደርጓቸው ነበርና በሚሞቱ ጊዜ ሲመሩባቸው የነበሩ ሰዎች ምስላቸውን ብንቀርፅ እነሱን እያስታወስን ዒባዳችን ላይ እንጠነክራለን በሚል ሀሳብ ቀረጿቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ሞተው ሌሎች ሲተኩ ግን ሸይጧን በስውር ገብቶ ከዚህ በፊት የነበሩ ሰዎች የሚያመልኳቸውና ዝናብም ሲጠፋ የሚማፀኗቸው እንደነበሩ አድርጐ በሀሰት መከራቸው እነሱም አመለኳቸው፡፡››[ተፍሲር አጠበሪ 12\254]
እነዚህ ሰዎች የፈፀሙት ሁለት አደጋዎችን በማጣመር ነበር፡-
አንደኛ፡- ቀብር ዘንድ በማክበር መቀመጥ::
ሁለተኛ፡- ምስላቸውን ቀርፆ ሲቀመጡበት በነበረበት ቦታ ላይ መትከል፡፡
በዚህ ሳቢያ በሰዎች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሽርክ ተከሰተ፡፡ እነዚህ ሁለት ነገሮች በየትኛውም ዘመንና ቦታ ላይ ትልቅ የሽርክ መንስኤ ናቸው፡፡
አላህ ከሽርክ ይጠብቀን!
No comments:
Post a Comment