Tuesday, 2 February 2016

PART 3 አንድ ጥያቄና አስር መልሶቹ!

     አንድ ጥያቄና አስር መልሶቹ!

(1-5) ያልተገለጠው እውነታ የተገለጠውን አይሽርም!
እኛ በቁርኣንና በሐዲሥ መረጃዎች የተረጋገጡ እውነታዎችን ያለ ምንም ቅሬታ እናፀድቃለን፤ በዝምታ የታለፉ ጉዳዮችን ደግሞ በዝምታ እናልፋለን! በእውቀት እንናገራለን፤ አሊያም ዝም! ይህ ነው የደጋጎቹ አበው መንገድ!
እናም አላህ ሰማያትንና ምድርን ፈጥሮ ሲያበቃ በዐርሹ ላይ ከፍ ማለቱን ነገረን እንጂ ዐርሹን ከመፈጠሩ በፊት የት እንደነበረ አላሳወቀንምና በመላ ምት አንዘላብድም!
አል-ቡኻሪይ እና ሌሎች እንደሚያስተላልፉት ታላቁ ታቢዒይ ሱለይማን አት-ተይሚይ (በ143 ዓ.ሂ ያረፉ) እንዲህ ብለዋል፦
لَوْ سُئِلْتُ أَيْنَ اللَّهُ؟ لَقُلْتُ: فِي السَّمَاءِ، فَإِنْ قَالَ: فَأَيْنَ كَانَ عَرْشُهُ قَبْلَ السَّمَاءِ؟ لَقُلْتُ: عَلَى الْمَاءِ، فَإِنْ قَالَ: فَأَيْنَ كَانَ عَرْشُهُ قَبْلَ الْمَاءِ؟ لَقُلْتُ: لَا أَعْلَمُ! قَالَ أَبُو عَبْدِ اللَّهِ: وَذَلِكَ لِقَوْلِهِ تَعَالَى: {وَلَا يُحِيطُونَ بِشَيْءٍ مِنْ عِلْمِهِ إِلَّا بِمَا شَاءَ} يَعْنِي: إِلَّا بِمَا بَيَّنَ
=› «“አላህ የት ነው?” ተብዬ ብጠየቅ “በሰማይ!” እላለሁ፤
“ከሰማይ በፊት ዐርሹ የት ነበር?” ቢለኝ “በውሃ ላይ!” እላለሁ፤  ከውሃ በፊት ዐርሹ የት ነበር?” ቢለኝ “አላውቅም!” እላለሁ።»
አቡ ዐብዲ’ላህ (አል-ቡኻሪይ - ከዘገባው ቀጥሎ) እንዲህ አሉ፦ «ይህም፦ {ከእውቀቱም እርሱ የሚሻውን እንጂ ምንም አያካልሉም (አል-በቀራህ 255)} በሚለው የአላህ ቃል (መሰረት) ነው፤ ማለትም፦ የገለፀውን እንጂ (አያውቁም)!»
[አል-ቡኻሪይ - “ኸልቁ አፍዓሊ’ል-ዒባድ” በተሰኘው መፅሐፋቸው 2ኛው ጥራዝ፣ ገፅ 38 ፣ ቁጥር 64፤ እንዲሁም አል-ላለካኢይ - “ሸርሑ ኡሱሊ’ዕቲቃዲ አህሊ’ስ-ሱን-ናህ..” 2ኛው ጥራዝ፣ ቅፅ 3 ፣ ቁጥር 671 ፤ ኢብኑ ቁዳማህ - “ኢሥባቱ ሲፈቲ’ል-ዑሉው” ገፅ 165 ቁጥር 75]
ስለዚህ ያላወቅነውን አለማወቃችን ያወቅነውን እንድናስተባብል ምክንያት ሊሆነን አይችልም! በድብቁ ምክንያትም ከግልፁ አንታወርም!
ያስተውሉ! ዐርሹ ከመፈጠሩ በፊት ስለነበረው ሁኔታ አለማወቃችን ከዚያ በኋላ ስላለው እውነታ በማስረጃዎች የፀደቀውን እምነት እንድናስተባብል አያደርገንም።
አል-ኢማም ዐብዱል-ዐዚዝ ኢብኑ’ል-ማጀሹን (በ164 ዓ.ሂ ያረፉ) እንደሚከተለው ብለዋል፦
«..فأَمَّا الَّذِي جَحَدَ مَا وَصَفَ الرَّبُّ مِنْ نَفْسِهِ تَعَمُّقًا وَتَكَلُّفًا فقَدِ اسْتَهْوَتْهُ الشَّيَاطِينُ فِي الْأَرْضِ حَيْرَانَ، فَصَارَ يَسْتَدِلُّ بزَعَمِهِ عَلَى جَحْدِ مَا وَصَفَ الرَّبُّ وَسَمَّى مِنْ نَفْسِهِ بِأَنْ قَالَ: لَا بُدَّ إِنْ كَانَ لَهُ كَذَا مِنْ أَنْ يَكُونَ لَهُ كَذَا! فَعَمِيَ عَنِ الْبَيِّنِ بِالْخَفِيِّ، وجَحَدَ مَا سَمَّى الرَّبُّ مِنْ نَفْسِهِ، بصَمْتِ الرَّبُّ عَمَّا لَمْ يُسَمِّ مِنْهَا..»
=›«..ጌታ ከራሱ ባህሪያት የገለፀውን ጠልቆ በመፈላፈልና በመፍጨርጨር ያስተባበለውማ ግራ የተጋባ ሆኖ ሰይጣኖች (አታልለው) በምድር ላይ መንገድ አስተውታል፤ በመሆኑም “እንዲህ ያለ ነገር ያለው ከሆነማ የግድ እንዲህ ያለ ነገርም ይኖረዋል..!” በማለት ጌታ ከራሱ ባህሪያት የገለፀውንና የሰየመውን ለማስተባበል በርሱ ቤት መረጃ ማቅረብ ያዘ! በድብቁ የተነሳ ከግልፁ ታወረ! ጌታ ስለ ራሱ ሳያወሳ በዝምታ ባለፋቸው (ዝርዝሮች) ምክንያትም ስለ ራሱ (በግልፅ) ያወሳውን ካደ!»
[ኢብኑ በጥ-ጠህ - “አል-ኢባነህ” (ሶስተኛው ክፍል) ጥራዝ 3 ገፅ 64፣ አዝ-ዘሀቢይ “አል-ዑሉዉ ሊል-ዐሊይ-ዪ’ል-ገፍ-ፋር” ገፅ 142 ቁጥር 386]
- በርግጥ ለጥያቄው ቀጥተኛ መልስ ሊሆን የሚችል መልዕክትን ያዘለ አንድ የሐዲሥ ዘገባ አለ። እርሱም እንደሚከተለው ይነበባል፦
عن أَبِي رَزِينٍ، قَالَ: قُلْتُ: يَا رَسُولَ اللهِ، أَيْنَ كَانَ رَبُّنَا - عَزَّ وَجَلَّ - قَبْلَ أَنْ يَخْلُقَ خَلْقَهُ؟ قَالَ: "كَانَ فِي عَمَاءٍ؛ مَا تَحْتَهُ هَوَاءٌ، وَمَا فَوْقَهُ هَوَاءٌ، ثُمَّ خَلَقَ عَرْشَهُ عَلَى الْمَاءِ".
=› «አቡ ረዚን እንዲህ ይላሉ፦ “የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ጌታችን ፍጥረታቱን ከመፍጠሩ በፊት የት ነበር?” አልኩኝ።
እርሳቸውም፦ “ ‘ዐማእ’ ውስጥ ነበር፤ ከላዩም ባዶ፣ ከስሩም ባዶ! ከዚያም ዐርሹን በውሃ ላይ ፈጠረ።” አሉ።» በአንደኛው የ“አል-በይሀቂይ” ዘገባ ላይ ደግሞ «ከዚያም በዐርሹ ላይ ሆነ!» የሚል ጭማሪ አለ።
[አሕመድ (ቁጥር 16188)፣ አት-ቲርሚዚይ (ቁጥር 3109)፣ ኢብኑ ማጀህ (ቁጥር 182)፣ አል-በይሀቂይ - “አል-አስማኡ ወስ-ሲፋት” ቁጥር 801 እና 864 እና ሌሎችም ዘግበውታል።]
“ዐማእ” ወይም “ዐማ” የሚለውን ቃል አንደኛው የሐዲሡ አስተላላፊ አል-ኢማም የዚድ ኢብኑ ሃሩን “ከርሱ ጋር ምንም ነገር የሌለበት” ሲሉ እንዳብራሩት አት-ቲርሚዚይ አያይዘው ጠቅሰዋል። ይህን ትርጓሜ የመረጡ እንዳሉ ሁሉ ከዚህ የተለየ ትርጉም የሰጡትም አሉ። [ለምሳሌ፦ “አል-አስማኡ ወስ-ሲፋት” ከቁጥር 864 ቀጥሎ፣ “አል-ተምሂድ” ጥራዝ 7 ገፅ 138፣ እንዲሁም “አን-ኒሃየቱ ፊ ገሪቢ’ል-ሐዲሥ” ጥራዝ 3 ገፅ 304 ይመልከቱ።]
- ሆኖም ይህ ዘገባ ጤናማ መሆኑ ያጠራጥራል፤ ምክንያቱም ሐዲሡን ከአቡ ረዚን (ለቂይጥ ኢብኑ ዓሚር) ያስተላለፈው የወንድማቸው ልጅ “ወኪዕ ኢብኑ ሑዱስ” (አንዳንዶች “ዑዱስ” ይሉታል) ሁኔታው ያልተጣራ “መጅሁል” እንደሆነ በርካታ የሐዲሥ ጠቢባን ፈርደዋልና። [ለምሳሌ፦ “ተህዚቡ’ት-ተህዚብ” የተሰኘውን የኢብኑ ሐጀር መፅሀፍ ጥራዝ 11 ገፅ 131 ይመልከቱ።]
ስለሆነም ምላሻችንን በመሰል አጠራጣሪ ወይም ደካማ ሰነድ ላይ አንመሰርትም። ይብላኝ ለነርሱ እንጂ!

No comments:

Post a Comment