Tuesday, 2 February 2016

PART 5 አንድ ጥያቄና አስር መልሶቹ!

    አንድ ጥያቄና አስር መልሶቹ!

(2-4) «..አላህ አሁንም ያለ ቦታ ነው!» የሚለው ገለፃ ደግሞ በሚከተሉት ነጥቦች ይብራራል፦
“ቦታ” የሚለው ቃል ሁለት አይነት ግንዛቤን ሊያስጨብጥ የሚችል በመሆኑ የተፈለገበትን መልዕክት ሳናጣራ በደፈናው ማፅደቅ ወይም ማፋረስ ተገቢ አይሆንም። ስለዚህም፦
1- “ቦታ” በፍጥረታት ክልል የተገደበ ግኝ ስፍራ ከታሰበበት በርግጥ አላህ ከፍጥረተ አለሙ ውጭ ነውና በእንዲህ ያለ “ቦታ” አይደለም!
ዐርሽ የፍጥረት ክልል ማብቂያ የመጨረሻው ጣሪያ ነውና! አላህ ከዐርሹ በላይ መሆኑን መናገር ደግሞ ይህንን አያስገነዝብም! በተለያዩ ቁርኣናዊና ነብያዊ ማስረጃዎች ላይ “በሰማይ” መሆኑ መነገሩ ደግሞ ስርወቃሉ በዐረብኛ ቋንቋ ጥቅል ከፍታን የሚጠቁም በመሆኑ እንጂ አላህ እንደ መላእክት በሰማያት ውስጥ የተገደበ እንደሆነ የሚያስብ አንድም ሙስሊም የለም!
2- ከቦታዎች ወሰን ውጭና ከፍጥረታት ክልል በላይ ያለው በአንፃራዊ ይዘቱ እንደ “ቦታ” ከታሰበ ደግሞ ቃሉን ፈርተን ብቻ ስፍር ቁጥር በሌላቸው መረጃዎች የተረጋገጠውን የበላይነቱን አናስተባብልም።

 በየትኛውም የአላህ፣ የመልዕክተኛውና የቀደምት ምርጥ ትውልዶች ንግግር ላይ ጭራሽ ባልተወሳው “አላሁ መውጁዱን ቢላ መካን!” (አላህ ያለ ቦታ ያለ ነው!) በሚለው የኑፋቄ መፈክር ተሸብረን እንዲህ ቁልጭ ያለ ሸሪዓዊና አእምሯዊ እውነታን አንጋፋም!
- እንዲያውም ስለ አላህ ከሁሉም ፍጡር ይበልጥ አዋቂ የሆኑት መልዕክተኛ የባሪያዪቱን አማኝነት ለማረጋገጥ “አላህ የት ነው?” ማለታቸው ይህን እውነታ አጉልቶ ያሳያል! [ሰሒሑ ሙስሊም ቁጥር (537) ይመልከቱ!]
በዚሁ አጋጣሚ “አላህ ያለ ቦታ ነው!” የሚለው መፈክር ከሙዕተዚላዎች የተወረሰ መሆኑን ለማረጋገጥ ከፈለጉ መቃላቱ’ል-ኢስላሚይ-ዪን” የተሰኘውን የአቡ’ል-ሐሰን አል-አሽዐሪይ መፅሐፍ ጥራዝ 1 ገፅ 286 ይመልከቱ!
- «አላህ በሁለተኛው መልእክት ላይ በተብራራው "ቦታ" ላይም አይደለም!» ካሉ ደግሞ ህልውናውን እያፋረሱ ነው!
የሚከተለው ነጥብ ይህን ይበልጥ ያጎላል፦

(2-5) ህልውና ወይስ ህሊናዊ?!

ልብ ይበሉ! የጥያቄው ውጤት የሚያመራው የፈጣሪን የበላይነት ወደ ማረጋገጥ እንጂ ወደ ማስተባበል ሊሆን አይችልም!
ለዚህም አል-ኢማም አሕመድ (241 ዓ.ሂ) በፅሁፋቸው ያሰፈሩትን የሚከተለውን አእምሯዊ እውነታ እናስተውል፦

قال الإمام أحمد ابن حنبل: وإذا أردت أن تعلم أن الجهميّ كاذبٌ على الله حين زعم أن الله في كل مكان، ولا يكون في مكان دون مكان، فقل له: أليس الله كان ولا شيء؟ فسيقول: نعم. فقل له: حين خلَقَ الشيءَ خلقَه في نفسه أو خارجًا من نفسه؟ فإنه يصير إلى ثلاثة أقاويل، لابد له من واحد منها:
إن زعم أن الله خَلَق الخلْق في نفسه فقد كفر، حين زعم أنه خلق الجن والشياطين وإبليس في نفسه.
إن قال: خلقهم خارجًا من نفسه ثم دخل فيهم، كان هذا كفرًا أيضًا حين زعم أنه دخل في كل مكان وحشٍ قذِر رديء.
وإن قال: خلقهم خارجًا عن نفسه، ثم لم يدخل فيهم، رجع عن قوله كلِّه أجمع، وهو قول أهل السنة.

=› «ጀህሚዩ አላህ በሁሉ ቦታ እንዳለና በአንድ ቦታ ሳይኖር በሌላ እንደማይሆን ሲሞግት በአላህ ላይ እየዋሸ መሆኑን ለማወቅ “አላህ ምንም ነገር ሳይኖር የነበረ አይደለምን?” በለው! እርሱም “ነበረ!” ይላል። “ነገሮችን በፈጠረ ጊዜ በራሱ ውስጥ ፈጠራቸው ወይስ ከራሱ ውጭ?” በለው። ያኔ ወደ ሶስት መልሶች ያመራል፤ ከነርሱ አንዱን ከመምረጥ ውጭ አማራጭ የለውም፦
1- አላህ ፍጡራንን በራሱ ውስጥ እንደፈጠራቸው ከሞገተ በርግጥ ይከፍራል፤ አጋንንትን፣ ሰይጣናትንና ኢብሊስን በውስጡ እንደፈጠረ ሞግቷልና!
2- “ከራሱ ውጭ ፈጥሯቸው ከዚያም በውስጣቸው ገብቷል!” ካለም ክህደት ነው፤ በአፀያፊ፣ በቆሻሻና በተልካሻ ቦታ ሁሉ እንደገባ ሞግቷልና!
3- “ከራሱ ውጭ ፈጥሯቸው ሲያበቃ በውስጣቸው አልገባም!” ካለ ደግሞ ከመጀመሪያው ንግግሩ መሉ በሙሉ ተመልሷል! ይኸኛውም የአህሉ’ስ-ሱና አቋም ነው!» [አሕመድ ኢብኑ ሐንበል - “አር-ረድ-ዱ ዐለ’ዝ-ዘናዲቀቲ ወ’ል-ጀህሚይ-ያህ” ገፅ 300-301]
ልብ ይበሉ! “አላህ አሁን ያለው ያኔ እንደነበረው ነው!” በሚለው ብንስማማ በላይኛው የኢማሙ ማብራሪያ መሰረት ከፍጥረተ አለሙ የቦታ ገደብ ውጭ መሆኑን አረጋገጥን ማለት ነው፤ አላህ ፍጡራኑን ያስገኘው ከራሱ ውጭ እንደሆነ ግልፅ ነውና! ከውጭ ከሆነ ደግሞ ከበላያቸው እንጂ ከበታች አይሆንም! እነዚያ ሙግተኞች ግን ከፍጥረተ አለሙ ውጭ መሆኑን ራሱ አይቀበሉም! የኢማሙ ጥያቄ እጅግ ቀላል ስሌት ሆኖ ሳለ የዘንድሮ ጀህሚያዎች የመረጡት የሽሽት መልስ ግን እንደ ሚስጥረ ስላሴ የተቋጠረ ነው! «በፍጥረተ አለሙ ውስጥ አይደለም፤ ከዚያ ውጭም አይደለም! ከላይም አይደለም፤ ከታችም አይደለም!..» ይሉናል።
- ለመሆኑ የአላህ ህልውና ህሊናዊ ብቻ ነው ወይስ እውን?
የቀድሞው የአሽዐሪይ-ያህ መንገድ እውነተኛ ጠንሳሽ የሆነው ኢብኑ ኩል-ላብ (243 ዓ.ሂ) እንኳ ያኔ እንዲህ ብሎ ነበር፦
وأَخْرَجُ من النظر والخبر قولُ من قال: لا هو في العالم ولا خارجٌ منه! فنفاه نفيًا مستويًا؛ لأنه لو قيل له: صفه بالعدم، ما قدر أن يقولَ فيه أكثرَ منه
«ከአእምሯዊ ምልከታም ከነጋሪት ማስረጃዎችም (ቁርኣንና ሐዲሥ) ይበልጥ ያፈነገጠው ደግሞ “በፍጥረተ-ዓለሙ ውስጥም አይደለም፤ ውጭም አይደለም!” በማለት (ሁለቱንም) እኩል የሚያፈርሰው ተናጋሪ ንግግር ነው! ምክንያቱም “(አላህን) ጭራሽ የማይገኝ በሆነ ኢምንትነት መገለጫ ግለፀው!” ቢባል ከዚህ የበለጠ ንግግር ሊናገር አይችልምና!»
[“በያኑ ተልቢሲ’ል-ጀህሚይ-ያህ” ጥራዝ 1ገፅ 44፣ “ደርኡ ተዓሩዲ’ል-ዐቅሊ ወን-ነቅል” ጥራዝ 6/119) (-ከኢብኑ ፉረክ እንዳተላለፉት)]
- አዎን! ይህ አፍራሽ ሀተታ «አላህ የለም!» ከሚለው መልዕክት የሚለይበትን ይዘት የሚያብራሩበት አንደበት የላቸውም! እንዲሁ ብቻ «አላሁ መውጁዱን ቢላ ከይፍ!» ማለትም፦ «አላህ ያለ ሁኔታ የሚገኝ ነው!» ወደሚል መፈክር ይጣደፋሉ! ያ የማይፈታ ትንግርታቸው የሚያሳድረውን አሉታዊ እንድምታ ለማለዘብ የመረጡት መሸሻ ይህ ነው። ይህን ንግግር አስመልክቶ ሶስት ነጥቦችን ለማንሳት እወዳለሁ፦
‪#‎አንደኛ፦ ማንኛውም ነገር የራሱ የሆነ ሁኔታ ሳይኖረው ገሀዳዊ ግኝት ሊኖረው አይችልም፤ ሊታሰብ ይችል ይሆናል፤ እውን ግን አይሆንም!
ለዚህም ነው ከጥንት ጀምሮ የኢስላም ሊቃውንት ስለ አላህና መገለጫዎቹ ሁኔታ “እንዴት” (ከይፍ) እያሉ መጠየቅን ያወገዙት ስለ ጉዳዩ ስላልተነገረንና አእምሯችንም ስለማይደርስበት እንጂ “አላህ ያለ ሁኔታ ያለ ነው!” በሚል መነሻ አይደለም!ለምሳሌ አል-ኢማም ዐብዱ’ል-ዐዚዝ አል-ማጀሹን (164 ዓ.ሂ) የአላህን ባህሪያት ስለሚያስተባብሉት ጀህሚያዎች በሰጡት ምላሽ ላይ የተናገሩትን እንደምሳሌ እንይ፦
وَإِنَّمَا يُقَالُ: كَيْفَ كَانَ؟، لِمَنْ لَمْ يَكُنْ مَرَّةً ثُمَّ كَانَ، فَأَمَّا الَّذِي لَا يَحُولُ، وَلَا يَزُولُ، وَلَمْ يَزَلْ، وَلَيْسَ لَهُ مِثْلٌ، فَإِنَّهُ لَا يَعْلَمُ كَيْفَ هُوَ إِلَّا هُوَ
=› « “እንዴት ሆነ?” የሚባለው እኮ አንድ ጊዜ ያልነበረ ሆኖ ከዚያ ስለሆነ ነገር ነው! ጭራሽ የማይለወጠው፣ የማይወገደው፣ ሁሌም የነበረውና አምሳያ የሌለው ግን እርሱ እንዴት እንዳለ ከርሱ በቀር የሚያውቅ የለም!»
[ኢብኑ በጥ-ጠህ - “አል-ኢባነህ” (ሶስተኛው ክፍል) ጥራዝ 3 ገፅ 64፣ አዝ-ዘሀቢይ “አል-ዑሉዉ ሊል-ዐሊይ-ዪ’ል-ገፍ-ፋር” ገፅ 141 ቁጥር 386]
- “አላህ ሁኔታ የለውም” ሳይሆን “እንዴት እንዳለ ከርሱ በቀር የሚያውቅ የለም!” ማለታቸው ይሰመርበት።
‪#‎ሁለተኛ፦ በቁርኣንና በሐዲሥ የተረጋገጡ የጌታ ባህሪያትን በጥቅሉ ማፅደቅ ሁኔታቸውን ከመግለፅ አይመደብም፤ ያ ሌላ ይሄ ሌላ! ያስተውሉ! ስለባህሪያቱ ዝርዝር ይዘትና ሁኔታ መናገርን ያወገዙት የአበው ሊቃውንት ራሳቸው እነዚያን ባህሪያት ያፀድቁ እንደነበር፤ ብሎም የማያፀድቁትን ሁሉ አጥብቀው ይኮንኑ እንደነበር የጥንቶቹ መዛግብት በሙሉ ይመሰክራሉ!
‪#‎ሶስተኛ፦ አል-ኢማም ኢብኑ ዐብዲ’ል-በር (463 ዓ.ሂ) ለመሰል ውዥንብር መልስ ሲሰጡ እንዲህ ይላሉ፦
فإِنْ قَالَ: إِنَّهُ لَا يَكُونُ مُسْتَوِيًا عَلَى مَكَانٍ إِلَّا مَقْرُونًا بِالتَّكْيِيفِ، قِيلَ: قَدْ يَكُونُ الِاسْتِوَاءُ وَاجِبًا وَالتَّكْيِيفُ مُرْتَفِعٌ، وَلَيْسَ رَفْعُ التَّكْيِيفِ يُوجِبُ رَفْعَ الِاسْتِوَاءِ، وَلَوْ لَزِمَ هَذَا لَزِمَ التَّكْيِيفُ فِي الْأَزَلِ؛ لِأَنَّهُ لَا يَكُونُ كَائِنٌ فِي لَا مَكَانٍ إِلَّا مَقْرُونًا بِالتَّكْيِيفِ، وَقَدْ عَقلْنَا وَأَدْرَكْنَا بِحَوَاسِّنَا أَنَّ لَنَا أَرْوَاحًا فِي أَبْدَانِنَا وَلَا نَعْلَمُ كَيْفِيَّةَ ذَلِكَ، وَلَيْسَ جَهْلُنَا بِكَيْفِيَّةِ الْأَرْوَاحِ يُوجِبُ أَنْ لَيْسَ لَنَا أَرْوَاحٌ! وَكَذَلِكَ لَيْسَ جَهْلُنَا بِكَيْفِيَّة "عَلَى عَرْشِهِ" يُوجِبُ أَنَّهُ لَيْسَ عَلَى عَرْشِهِ
=› «“(አላህ) ሁኔታው አብሮ ሳይገለፅ በ‘ቦታ’ ላይ መሆን አይችልም!” ካለ እንዲህ ይባላል፦
“ስለሁኔታው ጭራሽ የማይወሳ ሆኖ እያለ ‘ኢስቲዋእ’ (በዐርሹ ላይ መሆኑ) የፀና ይሆናል! ስለሁኔታው አለመወሳቱ የ‘ኢስቲዋእ’ መሻርን አያስከትልም! ይህ የግድ ቢሆን ኖሮ ዝንተ አለሙን (ፍጡራን ገና ሳይኖሩ በፊት) ስለ ነበረበት ሁኔታ ማውሳትን ያስከትል ነበር! ምክንያቱም ማንኛውም ነገር ሁኔታ ሳይኖረው ያለ ቦታም ሊኖር አይችልምና! መቼም በሰውነታችን ሩሕ (ነፍስ) እንዳለን ተገንዝበናል፤ በህዋሳችንም ደርሰንበታል! ስለ ሁኔታዋ ግን አናውቅም! ስለ ሩሓችን ሁኔታ አለማወቃችን ግን ሩሕ እንደሌለን አያመለክትም! ልክ እንዲሁ (አላህ) በዐርሹ ላይ የሆነበትን ሁኔታ አለማወቃችን በዐርሹ ላይ አለመሆኑን አያመለክትም!”»
[ኢብኑ ዐብዲ’ል-በር - “አት-ተምሂድ” ጥራዝ 7 ገፅ 137]

No comments:

Post a Comment