Tuesday, 2 February 2016

PART 1 አንድ ጥያቄና አስር መልሶቹ!

    አንድ ጥያቄና አስር መልሶቹ!
@ በሸይኽ ኢልያስ አህመድ
ይድረስ ለዐብዱ’ላሂ አል-ሀረሪ ተማሪዎችና ተከታዮች!

«በቁርኣን ውስጥ አላህ ከፍጥረታቱ በላይ እንዳለ የሚያመለክቱ አንድ ሺህ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ መረጃዎች አሉ!» 
[ከአንጋፋዎቹ የሻፊዒያህ መዝሀብ ሊቃውንት የአንዱ ንግግር ነው። (“መጅሙዑ’ል-ፈታዋ” ጥራዝ 5 ገፅ 121 ይመልከቱ።)]
የዚህ ፅሑፍ አላማ የአላህን የበላይነት የሚያረጋግጡ መረጃዎችን መዘርዘር አይደለም። ነገር ግን ይህንን እውነታ የማይቀበሉ ወገኖች የሚያነሱትን አንድ “ዝነኛ” ብዥታ ጠራርገው የሚያፀዱ ሸሪዓዊና አእምሯዊ ምላሾችን መጠቆም ነው። እንዲያውም የጥያቄያቸው ትክክለኛ ምላሽ የበላይነቱን የሚያፀና መሆኑን በስተመጨረሻ እናያለን! በትዕግስት ያንብቡት!
‪#‎ጥያቄ፦ 

«“አላህ በዐርሹ ላይ ነው!” ካላችሁ ዐርሽን ከመፍጠሩ በፊት የት ነበር?!»
-
በርግጥ አላህ ከዐርሽ በላይ የመሆኑን ብሩህ እውነታ በእንዲህ ያለ ጥያቄ መጋፈጥ እንደሚቻል የሚገምቱ ወገኖች ይህንን ጥያቄ የሚቀምሩት እንደሚከተለው ነው፦
«አላህ ዐርሽም ሆነ ሌላ ቦታ ሳይፈጠር የነበረ ጌታ ነው፤ እርሱ የማይቀያየር ጌታ በመሆኑ ዛሬም እንደያኔው ያለ ቦታ ነው ያለው!» ይላሉ።
[ይህ በተለያየ አገላለፅ የሚደጋግሙት ሀተታ “ዋነኛ መጋፈጫቸው” ነው፤ እንደ ምሳሌ፦ “አሽ-ሸርሑ’ል-ቀዊም” የተሰኘውን የዐብዱ’ላሂ አል-ሀረሪ መፅሐፍ ገፅ 212 (በአምስተኛው እትም መሰረት) መጥቀስ ይቻላል።]
#‎መልስ ፦
ይህን ድፍን ሙግት ከነመንደርደሪያው አንኮታኩተው የሚጥሉ ምላሾችን በሁለት መንገዶች ማቅረብ ይቻላል።
የመጀመሪያው መንገድ የጥያቄውን ስልት በጥቅሉ የተመለከቱ መሰረታዊ ምላሾችን ያካተተ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሙግቱ አሰካክ ላይ የሚያነጣጥሩ ዝርዝር ምላሾችን ያቀፈ ነው።
#‎አንደኛው_መንገድ፦ ስልቱን የተመለከቱ አምስት ጥቅል ምላሾችን ይዟል፤ እነሆ!
                                (1-1) እውነታ በውዥንብር አይረታ!

የአላህ ከበላይ መሆን በሸሪዓዊና አእምሯዊ አስረጆች የተረጋገጠ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ በሰዎች ተፈጥሯዊ ዝንባሌ ውስጥ ያሰረፀው አማራጭ የለሽ እምነት በመሆኑ ምንም አይነት ጥያቄን የሚያስተናግድ አይደለም! 
ልብ ይበሉ! በፅኑ መረጃዎች የፀደቀ እምነትን በማጠራጠሪያ መጠይቆች መጋፈጥ አይቻልም! ሙግት ደግሞ ማስረጃ አይሆንም! ማስረጃም በመላምት አይፈርስም! እውነታም በውዥንብር አይረታም።
ይህ ሙግት አል-ኢማም አዝ-ዘሀቢይ እና ሌሎች በትክክለኛ ሰነድ የዘገቡትን አንድ ተያያዥ ክስተት ያስታውሰናል፦
قال أَبُو جَعْفَر بن أبي عَليّ الْحَافِظ: سَمِعت أَبَا الْمَعَالِي الْجُوَيْنِيّ وَقد سُئِلَ عَن قَوْله {الرَّحْمَن على الْعَرْش اسْتَوَى} فَقَالَ: كَانَ الله وَلَا عرش وَجعل يتخبط فِي الْكَلَام فَقلت قد علمنَا مَا أَشرت إِلَيْهِ فَهَل عنْدك للضرورات من حِيلَة فَقَالَ مَا تُرِيدُ بِهَذَا القَوْل وَمَا تَعْنِي بِهَذِهِ الْإِشَارَة فَقلت مَا قَالَ عَارِف قطّ يَا رباه إِلَّا قبل أَن يَتَحَرَّك لِسَانه قَامَ من بَاطِنه قصد لَا يلْتَفت يمنة وَلَا يسرة يقْصد الفوق فَهَل لهَذَا الْقَصْد الضَّرُورِيّ عنْدك من حِيلَة فنبئنا نتخلص من الفوق والتحت وبكيت وَبكى الْخلق فَضرب الْأُسْتَاذ بكمه على السرير وَصَاح ياللحيرة وخرق مَا كَانَ عَلَيْهِ وانخلع وَصَارَت قِيَامَة فِي الْمَسْجِد وَنزل وَلم يجبني إِلَّا يَا حَبِيبِي الْحيرَة الْحيرَة والدهشة الدهشة فَسمِعت بعد ذَلِك أَصْحَابه يَقُولُونَ سمعناه يَقُول حيرني الْهَمدَانِي
=አል-ሓፊዝ አቡ ጀዕፈር ኢብኑ አቢ ዐሊይ አል-ሀመዛኒ (በ531 ዓመተ-ሂጅራ ያረፉ) እንዲህ ይላሉ፦ «አቡ’ል-መዓሊ አል-ጁወይኒ (478 ዓ.ሂ) “አር-ረሕማን ከዐርሹ በላይ ከፍ አለ” ስለሚለው የአላህ ንግግር ተጠይቆ “አላህ ዐርሽ ሳይኖር የነበረ ነው..” እያለ በንግግሩ ሲዘላብድ ሰማሁት! ከዚያም “ያመላከትከውን ነገር አውቀናል፤ ታዲያ ስለ “ዶሩሪያት” (እንድናረጋግጠው የግድ ስለሚለን ፅኑ እውነታ) መላ ቢጤ አለህን?” አልኩት። “በዚህ ንግግርህ ምን ፈልገህ ነው? በዚህ ጥቆማህስ ምን ወጥነህ ነው?” አለኝ። እኔም፦ “ማንኛውም አዋቂ ‘ጌታዬ ሆይ..!’ ካለ ገና ምላሱ ከመንቀሳቀሱ በፊት በውስጡ ፅኑ ስሜት ማደሩ አይቀሬ ነው፤ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሳይዞር እላይን ያስባል! ለዚህ ፅኑ እውነታ መላ አለህን? አሳውቀንና ከ‘ላይ’ እና ከ‘ታች’ እንገላገል!..” አልኩትና አለቀስኩ! ሁሉም አለቀሱ! መምህሩም (አል-ጁወይኒ) በእጅጌው አግዳሚ ቆጡን መታና “ወይ ግራ መጋባት!” ሲል ጮኸ! ልብሱንም ቀዶ ጣለ! በመስጂዱም ቂያማ ቆመ (ተረበሸ)! ከዚያም ወርዶ “ወዳጄ ሆይ! ኧረ ግራ መጋባት..! ኧረ መርበትበት..!” ከማለት ሌላ መልስ አልሰጠኝም። ከዚያም በኋላ ተማሪዎቹ “ ‘አል-ሀመዛኒ ግራ አጋባኝ!’ ብሎ ሲናገር ሰማነው!” ሲሉ ሰማኋቸው።»
[አዝ-ዘሀቢይ - “አል-ዑሉዉ ሊል-ዐሊይ-ዪ’ል-ገፍ-ፋር” ገፅ 259 ቁጥር 582 እንዲሁም “ሲየሩ አዕላሚ’ን-ኑበላእ” ጥራዝ 18 ገፅ 477፤ ኢብኑ ተይሚ-ያህ - “በያኑ ተልቢሲ’ል-ጀህሚይ-ያህ” ጥራዝ 1 ገፅ 51-52 ፤ አል-አልባኒ “በሑፋዞች ሰንሰለት የተያያዘ ትክክለኛ ሰነድ” እንደሆነ መስክረዋል። (“ሙኽተሰሩ’ል-ዑሉው” ገፅ 277 ይመልከቱ።)]
በጥቅሉ ስፍር ቁጥር በሌላቸው ማስረጃዎች የፀደቀውን የአላህ የበላይነት በመሰል ፀጉር ስንጠቃ መጋፋት ለአላህና ለመልዕክተኛው ንግግር ተገቢውን ቦታ ከመስጠት ጋር የሚጣረስ ነው!
                                        (1-2) ልዩነቱ ብርቱ!

ሌሎች ሙስሊሞች የአላህን የበላይነት ሲያፀድቁ እጅግ ብዙ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ቁርኣናዊና ነብያዊ አስተምህሮቶችን እያጣቀሱ ነው! እነዚያ ሙግተኞች ግን “አላህ ቦታ ሳይፈጠር የነበረ ነው፤ ዛሬም ያለ ቦታ ነው ያለው..» የሚለውን የዘወትር መፈክር የሚያትቱት በየትኛውም የቁርኣን ወይም የሐዲሥ መረጃ ወይም የሰሓቦች ንግግር ላይ አግኝተውት አይደለም! ይህን ማወቅ ብቻ ሙግታቸው ውድቅ መሆኑን ያረጋግጣል።
በርግጥ ይህንን ሙግት እንዲጠግን የተቀጠፈ መሰረተ ቢስ “ዘገባ” አይጠፋም!

ለምሳሌ፦ ታዋቂው የሐዲሥ ጠቢብ አል-ሓፊዝ ኢብኑ ሐጀር (852 ዓ.ሂ) «አላህ - ከርሱ ውጭ ምንም ነገር ሳይኖር ነበረ..» የሚለውን አል-ቡኻሪይ ዘንድ በቁጥር 3191 ላይ የሚገኘውን ሐዲሥ ባብራሩበት አጋጣሚ እንዲህ ብለዋል፦

تَنْبِيهٌ: وَقَعَ فِي بَعْضِ الْكُتُبِ فِي هَذَا الْحَدِيثِ: كَانَ اللَّهُ وَلَا شَيْءَ مَعَهُ، وَهُوَ الْآنَ عَلَى مَا عَلَيْهِ كَانَ! وَهِيَ زِيَادَةٌ لَيْسَتْ فِي شَيْءٍ مِنْ كُتُبِ الْحَدِيثِ! نَبَّهَ عَلَى ذَلِكَ الْعَلَّامَةُ تَقِيُّ الدِّينِ بْنُ تَيْمِيَةَ، وَهُوَ مُسَلَّمٌ فِي قَوْلِهِ وَهُوَ الْآنَ إِلَى آخِرِهِ

=› «ማሳሰቢያ፦ በሆነ መፅሀፍ ውስጥ በዚህ ሐዲሥ ላይ “አላህ - ከርሱ ጋር ምንም ሳይኖር ነበረ፤ ‘እርሱ አሁንም ያኔ በነበረበት ላይ ነው!’ ” የሚል (ገለፃ) ሰፍሯል! ይህ በየትኛውም የሐዲሥ መፃህፍት ላይ የማይገኝ ጭማሪ ነው! ይህንን ታላቁ ዓሊም ተቂይ-ዩ’ድ-ዲን ኢብኑ ተይሚይ-ያህ አስገንዝቧል። ይህም “..እርሱ አሁንም ያኔ በነበረበት ላይ ነው!” የሚለውን አስመልክቶ እጅ የሚሰጥለት ነው..»

[ኢብኑ ሐጀር - “ፈትሑ’ል-ባሪ” ጥራዝ 6 ገፅ 289] [በተጨማሪም “መጅሙዑ’ል-ፈታዋ” ቅፅ 2 ገፅ 272 እንዲሁም “ከሽፉ’ል-ኸፋእ..” የተሰኘውን የአል-ዐጅሉኒ መፅሃፍ ቁጥር 2011 ይመልከቱ።]
በተመሳሳይ መልኩ ታላቁ ሰሓቢይ ዐሊይ ኢብኑ አቢ ጣሊብ ይህን መሰል ቃል እንደተናገሩ የሚወራ ቅጥፈት አለ፦
قد كان ولا مكان، وهو الآن على ما كان
ትርጉሙም፦ «በርግጥ ቦታ ሳይኖር ነበር፤ እርሱ አሁንም ያኔ በነበረበት ላይ ነው!»
ይህ ንግግር የአሽዐሪያህ አቀንቃኙ ዐብዱ’ል-ቃሂር አል-በጝዳዲይ [አል-ኸጢብ አል-በጝዳዲይ (463 ዓ.ሂ) አለመሆኑን እያስተዋሉልኝ!] «አል-ፈርቁ በይነ’ል-ፊረቅ» በተሰኘው መፅሀፍ ገፅ 321 ላይ ያለ ምንም የሰነድ ልጓም ያሰፈረው ልቅ ወሬ ነው! ዐሊይ የሞቱት በ40ኛው አመተ ሂጅራ ሲሆን ዐብዱ’ል-ቃሂር አል-በጝዳዲይ የሞተው ደግሞ በ429 ዓመተ ሂጅራ ነው። ስለዚህ በመካከላቸው ከሞላ ጎደል የአራት ክፍለ ዘመናት ክፍተት አለ፤ ወሬው ደግሞ ይህ ሰፊ የምእተ አመታት ርቀት የሚያያዝበት የዘገባ ሰንሰለት የለውም!
ታላቁ የኢስላም ሊቅ ዐብዱ'ላህ ኢብኑ'ል-ሙባረክ (181 ዓ.ሂ) እንዲህ ይላሉ፦
«الْإِسْنَادُ مِنَ الدِّينِ، وَلَوْلَا الْإِسْنَادُ لَقَالَ مَنْ شَاءَ مَا شَاءَ»
=› «"ኢስናድ" (ሐዲሥ ወይም ሌላ ዘገባ ከአንድ ሰው ወደሌላ የሚተላለፍበት የቅብብሎሽ ሠንሠለት) የዲን አካል ነው፤ "ኢስናድ" ባይኖር ኖሮ ማለት የፈለገ ሁሉ ያሻውን ባለ ነበር!»

 በተጨማሪም እንዲህ ብለዋል፦
بَيْنَنَا وَبَيْنَ الْقَوْمِ الْقَوَائِمُ - يَعْنِي: الْإِسْنَادَ-.
=› «በኛና በሌሎቹ መካከል (የሚዳኝ) "ኢስናድ" አለ!»
[ሁለቱም በሶሒሕ ሙስሊም መግቢያ ላይ (ጥራዝ 1 ገፅ 15) የሰፈሩ ትክክለኛ ዘገባዎች ናቸው!]
አዎን! የላይኛው ቅጥፈት እውነተኛ ምንጮች በተለያዩ የእምነት አጀንዳዎች ላይ ግልፅ ክህደትን በማራመድ እንዲሁም ውሸቶችን በማቀናበርና በመንዛት የሚታወቁት “ራፊዷዎች” ስለመሆናቸው አንዳንድ መፅሐፎቻቸው ይመሰክራሉ። [ለምሳሌ “አል-ካፊ” የተባለውን የኩለይኒ መፅሐፍ ቅፅ 1 ገፅ 90 ይመልከቱ።]
ትክክለኛ ሐዲሦችን “ኣሓድ” (በበርካታ መንገዶች ያልተዘገቡ) በመሆናቸው ብቻ በእምነት ርእሶች ላይ ከመቀበል እየታቀቡ በአንፃሩ ትክክለኛ ሊሆኑ ይቅርና ለደካማነት እንኳ ባልበቁ ውዳቂ አፈ ታሪኮች ላይ እምነታቸውን ይመሰርታሉ! አልፎም ሸሪዓዊ እውነታዎችን ይፃረራሉ! አላህ እውነታውን ይግለጥላቸው!

No comments:

Post a Comment