አንድ ጥያቄና አስር መልሶቹ!
በመጨረሻም ከላይኛው ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚነሳ አንድ የተለመደ መፈክር አለ፦ «አላህ ዐርሽ ወይም ሌላ ቦታ አያስፈልገውም!»
ይህን አስመልክቶ ሁለት መልሶችን ብቻ እንጥቀስ፦
#1ኛ፦ አላህ ከዐርሹ በላይ የሆነው ቦታ ስለሚያስፈልገው እንደሆነ የሞገተ አንድም ሙስሊም ሳይኖር ይህንን ክርክር ማንሳት ከንቱ ነው፤ ከርዕሱ የወጣም ዛዛታ ነው!
አላህ ከማንኛውም ፍጡር ምንም አይነት እርዳታ የማይፈልግ ተብቃቂ ጌታ ነው! ዐርሽን፣ ሰማያትንና ምድርን እንዲሁም መላ ፍጡራንን በወሰን-የለሽ ችሎታው የሚቆጣጠረውና የሚያስተናብረው ማን ሆነና?! ያለ እርሱ እርዳታ የትኛውም ፍጡር ሊኖርም ሆነ ሊቆም መች ይችልና?! ሃያሉ አምላካችን ልቅናና ጥራት የተገባው ነው!
إِنَّ ٱللَّهَ يُمۡسِكُ ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَٱلۡأَرۡضَ أَن تَزُولَاۚ وَلَئِن زَالَتَآ إِنۡ أَمۡسَكَهُمَا مِنۡ أَحَدٖ مِّنۢ بَعۡدِهِۦٓۚ إِنَّهُۥ كَانَ حَلِيمًا غَفُورٗا
= «አላህ ሰማያትንና ምድርን እንዳይወገዱ ይይዛቸዋል፤ ቢወገዱ ከርሱ ሌላ አንድም የሚይዛቸው የለም! እነሆ እርሱ ሁሌም ታጋሽ መሀሪ ነውና።» [ፋጢር 41]
ግን ይህ የሚያሳየው ጀህሚያዎችና ተከታዮቻቸው በቁርኣንና በሱን-ናህ የተረጋገጡትን የጌታ ባህሪያት መልዕክት እንዲቆለምሙ ያደረጋቸው ቀድሞውኑ የመረጃዎቹን መልዕክት የተረዱት የፍጡራን ባህሪያትን በሚረዱበት ይዘት መሆኑን ነው!
ለምሳሌ፦ አላህ በዐርሹ ላይ መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ሲሰሙ የሚገነዘቡት መልዕክት አንድ ፍጡር በሌላ ነገር ላይ መሆኑን በሚገነዘቡበት ይዘት ስለሆነ “አላህ ከዐርሽ በላይ ከሆነ ለርሱ ዐርሽ ያስፈልገዋል ማለት ነው! ዐርሽ ይሸከመዋል ማለት ነው! ..ወዘተ” በሚል ፈሊጥ የበላይነት መገለጫውን ወደማፋረስ አቀኑ! አዎን! እነርሱ ናቸው አመሳሳዮቹ! ቀድሞውኑ ይህን የፍጡር መገለጫ ከማስረጃዎቹ የሚረዳው ህሊናው በማመሳሰል አባዜ የተበከለ ብቻ ነውና!
ይህንና ሌሎች ትክክለኛ መገለጫዎቹን ያለ ምንም አጉል ፈሊጥ ለጌታ ማንነት በሚገባው መልኩ የሚያፀድቁት ሌሎች ሙስሊሞች ግን አላህ ከእንደዚህ አይነት ጉድለት የጠራ መሆኑን አስቀድመው ስለሚያምኑ መረጃዎቹን ማጣመም አላስፈለጋቸውም!
#2ኛ- አላህ በጥበቡ የሚፈፅማቸውን አድራጎቶች በእንዲህ ያለ ሰንካላ መነሻ መጋፈጥ አያስኬድም!
አላህ ማንኛውንም ነገር በአንድ ቃል በቅፅበት ማከናወን የሚችል ሃያል ጌታ ከመሆኑ ጋር በጥበቡ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀናት ፈጥሯል። ታዲያ እርሱ ምንም የሚሳነው ባለመሆኑ ብቻ የስድስት ቀናቱን እውነታ እናስተባብላለን?!
እንዲሁም አላህ የማንም እገዛ ሳያስፈልገው ሁሉን ማከናወን የሚችል ከመሆኑ ጋር የተለያዩ የፍጥረተ አለም ክንውኖችን በርሱ ፈቃድ የሚያስተናብሩ መላእክትን ፈጥሯል። ታዲያ እርሱ እገዛ የሚያስፈልገው ባለመሆኑ የመላኢካን ህልውና እንክዳለን?!
ለእንዲህ አይነት ጥያቄ በር ከተከፈተ በአንፃሩ ደግሞ ማብቂያ የሌላቸው ምሳሌዎችም ይዥጎደጎዳሉ!
ያሳለፍናቸውን ነጥቦች በአጭሩ እንከልሳቸው፦
*ጥቅል ምላሾቹ አምስት ሲሆኑ እነርሱም እንደሚከተለው ይቀርባሉ፦
1- የአላህ ከበላይነት በፅኑ ማስረጃዎች የተረጋገጠ በመሆኑ ጥያቄን አያስተናግድም!
2- በአንፃሩ ደግሞ ይህ ሙግት በየትኛውም መረጃ ላይ አይገኝም!
3- መሰል ጥያቄዎችን ማንሳት የተወገዘ ፈጠራ ነው!
4- ተውሒድ በንፅፅራዊ አመክንዮ አይለካም!
5- ያላወቅነው እውነታ ያወቅነውን አይሽርም!
*ዝርዝር ምላሾቹ ደግሞ ባጭሩ የሚከተሉት ነበሩ፦
1- «ቅድሚያ የት ነበር?!» የሚለው ቃና ራሱ ስህተት ነው! ምንም ባልነበረበት ከምን በላይ ነበር ይባላል?!
2- «ዐርሽም ሆነ ሌላ ቦታ ሳይፈጠር የነበረ ጌታ ነው!..» የሚለው ደግሞ ከዐርሹ በላይ ከመሆኑ ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አይጋጭም!
3- «..የማይቀያየር ጌታ ስለሆነ..» የሚለው ደግሞ የማሸማቀቂያ ስልት እንደሆነና ከዐርሹ በላይ መሆኑ በየትኛውም ቋንቋ "መቀየር" ተብሎ እንደማይጠራ፣ ያንንም የሚያስገነዝብ እንዳልሆነ ተብራርቷል።
4- «አሁንም እንደያኔው ያለ ቦታ ነው..» የሚለው አሻሚ ቃል ደግሞ "ቦታ" የፍጡራን ክልል ውስጥ ያለ ግኝ ስፍራ ከታሰበበት ያስማማናል፤ ከቦታዎች ክልል ውጭ ያለው በአንፃራዊ ገለፃ "ቦታ" ከተሰኘ ደግሞ ቃሉን ፈርተን የበላይነቱን አናስተባብልም!
5- የአላህ ህልውና እውን መሆኑን ካመኑ ፍጡራኑን ያስገኘው ከራሱ ውጭ ነውና ሁሌም ከበላያቸው እንጂ ከበታች እንደማይሆን ሊያረጋግጡ የግድ ይላል!
*በመጨረሻም "አላህ ቦታ አያስፈልገውም!" የሚለው ነጥብ ውዝግብ የሌለበት መሆኑንና በዐርሹ ላይ መሆኑ መገለፁም ይህንን ጉድለት የሚያስገነዝብ እንዳልሆነ በምሳሌዎች ቃኝተናል!
ለጊዜው ጨርሻለሁ!
@ በሸይኽ ኢልያስ አህመድ
No comments:
Post a Comment