Tuesday, 2 February 2016

PART 4 አንድ ጥያቄና አስር መልሶቹ!

    አንድ ጥያቄና አስር መልሶቹ!

ሁለተኛው መንገድ (የሙግቱ አሰካክ ላይ ያነጣጠረ ዝርዝር ምላሽ)
«“አላህ በዐርሹ ላይ ነው!” ካላችሁ ዐርሽን ከመፍጠሩ በፊት የት ነበር?!» «ዐርሽም ሆነ ሌላ ቦታ ሳይፈጠር የነበረ ጌታ ነው፤ እርሱ የማይቀያየር በመሆኑ ዛሬም እንደያኔው ያለ ቦታ ነው ያለው!»
የሚለውን የሙግት አሰካክ በታትነን እንመርምረው፦
(2-1) በቅድሚያ «“አላህ በዐርሹ ላይ ነው!” ካላችሁ ዐርሽን ከመፍጠሩ በፊት የት ነበር?!» የሚለው ቃና ራሱ ስህተት ነው፤ ምክንያቱም “የት” የሚለው ጥያቄ መልስ የሚያገኘው ለገለፃ የሚያግዝ መነሻ (reference) ሲኖር ነው! ለዚህም ነው “አላህ የት ነው?” ሲባል፦ “ከዐርሹ በላይ፣ ከፍጥረተ-ዓለሙ ውጭ፤.. ወዘተ” የምንለው። በዚህ ገለፃ ላይ ዐርሽን ወይም አጠቃላይ ፍጥረተ አለሙን እንደ መነሻ በማጣቀስ የአላህ የበላይነትን አውስተናል። ሆኖም ዐርሽም ሆነ ሌላ ፍጡር ጭራሽ ባልነበረበት ሁኔታ አላህ የት እንደነበር በምን ቋንቋ መመለስ ይቻላል? ከምንስ በላይ ነበር ይባላል?
ልብ ይበሉ! የህልውናው የበላይነት (ዑሉው) ከማንነቱ የማይነጠል የዝንተ አለም መገለጫው ነው! ዐርሹን ከፈጠረ በኋላ በርሱ ላይ መሆኑ (ኢስቲዋእ) ደግሞ ይህንን የሚያጎላ አድራጎታዊ መገለጫ ነው።
- ደግሞም ከላይ እንደተብራራው የማናውቀው እውነታ የምናውቀውን አይሽርም!
(2-2) «አላህ ዐርሽም ሆነ ሌላ ቦታ ሳይፈጠር የነበረ ጌታ ነው!..» የሚለውን መነሻ ከመልዕክት አንፃር ስንፈትሸው ደግሞ፦
- ይህ በመሰረቱ የውዝግብ ርዕስ አይደለም፤ ሆኖም አላህ ከዐርሹ በላይ ከመሆኑ እውነታ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጋጭ ባለመሆኑ በዚህ ሂደት መጠቀሱ ምንም አይፈይድም!
ይህን ይበልጥ የሚያብራራው ደግሞ ቀጣዩ ነጥብ ነው፦
(2-3) «እርሱ የማይቀያየር ጌታ ስለሆነ..» የሚለውን ገለፃ በተመለከተ ደግሞ ጥቂት ነጥቦችን አብረን እንቃኝ፦
‪#‎ሀ- በቁርኣንና በሐዲሥ የተረጋገጡትን የጌታ ባህሪያት በሚያጠራጥር ወይም በሚያሳቅቅ ቃል መግለፅ እውነታውን አይቀይረውም፤ ልብ ይበሉ!

 አል-ኢማም አሕመድ (241 ዓ.ሂ) እንዲህ ብለው ነበር፦
..وَلَا نُزِيلُ عَنْهُ صِفَةً مِنْ صِفَاتِهِ لشَنَاعَةٍ شُنِّعَتْ..
=› «የሚፀየፍ ተፀይፎ ስላወገዘ (ብለን) ከባህሪያቱ አንዱንም አናስወግድም!»
[ኢብኑ በጥ-ጠህ - “አል-ኢባና” ጥራዝ 3 ገፅ 326፣ ኢብኑ ቁዳማህ - “ዘም-ሙ’ት-ተእዊል” ገፅ 22]
‪#‎ለ- “መቀየር” ፣ “መለወጥ” እና መሰል ቃላት በዚህ ሂደት የሚፈለግባቸው ፍልስፍናዊ ይዘታቸው እንጂ ቋንቋዊው መልዕክታቸው አለመሆኑን ማወቅ የግድ ይለናል። በዚህም መሰረት የላይኛው ሙግት ባለቤቶች የአላህን ከዐርሹ በላይ መሆን ብቻ ሳይሆን እርሱ በሚሻ ጊዜ የሚፈፅማቸውን አድራጎታዊ መገለጫዎች በሙሉ በ“መቀየር” እና በ“ክስተት” ስም ውድቅ ያደርጋሉ!
ለምሳሌ፦ በፈለገው ጊዜ መናገሩን “‘ክስተት’ ነው!” በማለት ያጣጥሉታል፤ በቁርኣኑ እንዳፀደቀው በእለተ-ቂያማህ ለፍርድ መምጣቱን “እንቅስቃሴ ነው..!” ሲሉ ያስተባብሉታል። ምክንያቱን ሲያብራሩ ደግሞ «መንቀሳቀስም ሆነ አለመንቀሳቀስ ሁለቱም ክስተት ናቸው! ክስተት ደግሞ መቀየር ነው! ፈጣሪ ደግሞ አይቀየርም!..» ይላሉ።
- በመሰረቱ እኛ በቁርኣንና በሐዲሥ የሌሉ አሻሚ ገለፃዎችን በአዎንታዊም ይሁን በአፍራሽ መልኩ አንጠቀምም! በቃ! በእምነታችን ላይ የቁርኣንና የሐዲሥ ገለፃን አንተላለፍም! እንደ “ክስተት” እና “መቀየር” ያሉ ቃላት እውነታን በሚጥስ መልኩ ለሚታለመው ውጤት እንዲውሉ የሚቆለመሙና ከቋንቋዊ ይዘታቸው የወጡ መልዕክቶች የሚታጨቁባቸው አሻሚ ገለፃዎች ናቸውና!
- በዚህ ላይ ደግሞ መናገርም ይሁን መንቀሳቀስና አለመንቀሳቀስ “መቀየር” መሆናቸው የነሱ ፍልስፍናዊ አጠራር እንጂ ሌሎች ባለ አእምሮዎች የሚስማሙበት እንዳልሆነ ግልፅ ነው!
- እንደሚታወቀው በየትኛውም ቋንቋ አንድ ነገር “ተቀየረ” የሚባለው ከቀድሞው ይዘቱ የተለየ አዲስ መገለጫ ሲኖረው ነው።
ለምሳሌ፦ አንድ ሰው በበሽታ ምክንያት ሲከሳ ወይም ሲጠቁር ፣ ወይም አርጅቶ ፀጉሩ ሲሸብት አሊያም በምቾት ሲወፍር ወይም ሲቀላ “ተቀየረ” ይባላል። ስነ ምግባሩ ሲሻሻል ወይም ሲበላሽም “ተቀየረ” ይባላል።
የአየሩ ሙቀት ከተለመደው በላይ ከፍ ወይም ዝቅ ሲል እንዲሁም ምግብ ሲሻግት ወይም ጠረኑ ሲለወጥ አሊያም የመጠጥ ቀለም ይዘቱን ሲለቅ እንደዚሁ “ተቀየረ” ይባላል። ወዘተ...
በአንፃሩ ደግሞ አንድ ሰው መናገር ሲጀምር ወይም ተናግሮ ዝም ሲል፣ ወይም ሲቆም አሊያም ሲቀመጥ፣ በጥቅሉ ሲንቀሳቀስና እስቅስቃሴውን ሲተው ከልማዱ እስካልወጣ ድረስ “ተቀየረ” አይባልም። በጥቅሉ አንድን ድርጊት ስለፈፀመ ብቻ ድርጊቱ እንደ “መቀየር” አይታሰብም፤ በዚህ ቃልም አይገለፅም!
[ለተጨማሪ ማብራሪያ “ደርኡ ተዓሩዲ’ል-ዐቅሊ ወን-ነቅል” ጥራዝ 4 ገፅ 72-75 እንዲሁም “መጅሙዑ’ል-ፈታዋ” ቅፅ 6 ገፅ 249-250 ይመልከቱ።]
በዚህ መሰረት “አላህ አይቀያየርም!” ሲባል የህልውናው የበላይነት መቼም የማይለወጥ፣ የባህሪያቱ ምጥቀት መቼም የማይከስም፣ ዘልአለማዊነቱ የማይቋረጥ፣ እንደፍጡራን የጉድለት ክስተቶችን የማያስተናግድ ፍፁም መሆኑን ለማሳየት ከሆነ ትክክለኛ መልዕክት ይሆናል።
እነዚያ ሙግተኞች ይህን የሚሉት ግን ይህን ጉልህ መልዕክት ወጥነው አይደለም! አዎን! “ፈጣሪ አይቀያየርም!” ሲሉ የሰማ የዋህ ለጌትነቱ ከማይገቡ ጉድለቶችና ጠንቆች እያላቁት ይመስለው ይሆናል! እውነታው ግን የ“መቀየር”ን የታወቀ መልዕክት በመቀየር አላህ ስለራሱ ያፀደቃቸውን እውነታዎች እየቀየሩ፣ አድራጊነቱንም እየገደቡ መሆናቸው ነው! አዎን! በአሻሚ ገለፃዎች ተከልለው በቁርኣን የተረጋገጡ መገለጫዎቹን ይንዳሉ!
ሙስሊሞች እንደ ንግግር፣ መፍጠር፣ ለፍርዱ መምጣት፣ ከዐርሹ ላይ መሆን ያሉ መሰል አድራጎታዊ የጌታ መገለጫዎችን እንደ መቀየር እንደማያስቡ ግልፅ ነው።
የፍጡር አድራጎት እንኳ መቀየር ካልሆነ የአላህ አድራጎት ሁኔታ ጭራሽ በአእምሮ የማይደረስበትና ከፍጡራን ሁኔታ እጅግ የተለየና የላቀ መሆኑ እየታወቀ እንዴት በ“መቀየር” ይገለፃል?!
እንደሚታወቀው ፍጥረታት ከመፈጠራቸው በፊትና ከተፈጠሩ በኋላ ያለው ልዩነት በቀጥታ የሚመለከተው ፈጣሪን ሳይሆን ፍጡራንን ራሳቸውን ነው! የፍጡራን ህልውና ካለመኖር ወደ መኖር በመሸጋገሩ የአዲስነት ክስተትን አስተናግዷል። አላህ ግን ሁሌም ፈጣሪ፣ ሁሌም የሻውን አድራጊ ከመሆን አልተወገደም! ያኔ ብቻውን የነበረ መሆኑ፣ አሁን ደግሞ ፍጡራን በመኖራቸው ከነርሱ በላይ መሆኑ የማንነት ለውጥ ነውን?
ከላይ እንዳየነው የህልውናው የበላይነት (ዑሉው) ከማንነቱ የማይነጠል የዝንተ አለም መገለጫው ነው! ዐርሹን ከፈጠረ በኋላ በርሱ ላይ መሆኑ (ኢስቲዋእ) ደግሞ ይህንን የሚያጎላ አድራጎታዊ መገለጫ እንጂ መቀየር አይደለም!
ስለሆነም የአላህ ከዐርሹ በላይ መሆን ከመቀየር ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚዛመድበት መንገድ የለምና በባዶ ማስፈራሪያ ፅኑ መለኮታዊ እውነታን መፃረር አይቻልም!
ደግሞም፦
‪#‎ሐ- አላህ የሻውን ሁሉ ማድረጉ የምሉእነቱ መገለጫ እንጂ ጉድለት ሊሆን አይችልም! እንዲያውም አድራጊ የሆኑ ነገሮች አድራጊ ባልሆኑት ላይ መሰረታዊ ብልጫ እንዳላቸው የማንም አእምሮ አይክድም! ስለሆነም ይህንን ፅኑ እውነታ በአሻሚ ቃላት መናድ አይቻልም!
ታዋቂው የኢስላም ሊቅ አል-ፉደይል ኢብኑ ዒያድ (187 ዓ.ሂ) እንዲህ ይላሉ፦
«إِذَا قَالَ لَكَ جَهْمِيٌّ: أَنَا أَكْفُرُ بِرَبٍّ يَزُولُ عَنْ مَكَانِهِ، فَقُلْ: أَنَا أُؤْمِنُ بِرَبٍّ يَفْعَلُ مَا يَشَاءُ»
«አንድ ጀህሚይ “እኔ ከቦታው በሚወገድ ጌታ እክዳለሁ!” ካለህ “እኔ ደግሞ የሻውን በሚሰራ ጌታ አምናለሁ!” በል!»
[አል-ቡኻሪይ - “ኸልቁ አፍዓሊ’ል-ዒባድ” ጥራዝ 2 ገፅ 36 ቁጥር 61፣ ኢብኑ በጥ-ጠህ - “አል-ኢባናህ” (ሶስተኛው ክፍል) ጥራዝ 3 ገፅ 204፣ አል-ላለካኢይ - “ሸርሑ ኡሱሊ’ዕቲቃዲ አህሊ’ስ-ሱን-ናህ” ጥራዝ 2 ቅፅ 3 ገፅ 452]
እንዲሁም አል-ኢማም ኢስሓቅ ኢብኑ ራሀወይህ (238 ዓ.ሂ) እና አል-ኢማም የሕያ ኢብኑ መዒን (233 ዓ.ሂ) ተመሳሳይ ንግግር አስፍረዋል።
[ኢብኑ በጥ-ጠህ - “አል-ኢባናህ” (ሶስተኛው ክፍል) ጥራዝ 3 ገፅ 206፣ አል-ላለካኢይ - “ሸርሑ ኡሱሊ’ዕቲቃዲ አህሊ’ስ-ሱን-ናህ” ጥራዝ 2 ቅፅ 3 ገፅ 453፣ አል-በይሀቂይ - “አል-አስማኡ ወ’ስ-ሲፋት” ጥራዝ 2 ገፅ 375-376፣ አዝ-ዘሀቢይ - “ሲየሩ አዕላሚ’ን-ኑበላእ” ጥራዝ 11 ገፅ 376]
ስለዚህ በመሰል ስልቶች ቁርኣናዊ እውነታን መጋፋት መረጃዎችን ከማጣመም በቀር የሚፈይደው ትርፍ የለም!


No comments:

Post a Comment