አንድ ጥያቄና አስር መልሶቹ!
(1-3) ቢድዓ ነው!
በእምነት ጉዳይ ላይ ይህ አይነቱን ጥያቄ ማንሳት የተወገዘ ፈጠራ (ቢድዓህ) ነው! ምክንያቱም የህዝበ-ሙስሊሙ አርዓያ የሆኑት ቀደምት ትውልዶችና ታላላቅ መሪዎች ይህን መሰል ጥያቄ አንድም ቀን አንስተው አያውቁም! ጥያቄውን ማንሳት ለእምነት የሚፈይድ ቢሆን እነርሱ በቀደሙን ነበር! ያኔ ያልነበረ የእምነት ድርሻ ስለማይተርፍልን በነርሱ ፋና ላይ ከመጓዝ ያለፈ አማራጭ የለንም።
› አል-ኢማም ማሊክ (179 ዓ.ሂ) እንዲህ ብለዋል፦
إياكم والبدع، قيل: يا أبا عبد الله وما البدع؟ قال: أهل البدع الذين يتكلمون في أسماء الله وصفاته وكلامه وعلمه وقدرته، لا يسكتون عما سكت عنه الصحابة والتابعون
=› «ቢድዓዎችን አደራችሁን! (ተጠንቀቁ!)» ሲሉ «የዐብዱ’ላህ አባት ሆይ! ቢድዐዎች ምንድናቸው?» ተብለው ተጠየቁ። እርሳቸውም፦
«የቢድዓህ ባለቤቶች! እነዚያ ስለ አላህ ስሞችና ባህሪያት፣ ስለ ንግግሩ፣ እውቀቱና ችሎታው የሚናገሩና ሰሓቦችና ታቢዒዮች በዝምታ ያለፉትን በዝምታ የማያልፉ!» ብለው መለሱ።
[አቡ ዑሥማን አስ-ሷቡኒ - “ዐቂደቱ’ስ-ሰለፍ ወአስሓቢ’ል-ሐዲሥ” ገፅ 244 ፣ አቡ ኢስማዒል አል-ሀረዊ “ዘም-ሙ’ል-ከላሚ ዋህሊሂ” ቅፅ 5 ገፅ 70 ቁጥር 858]
ስለሆነም ቀደምት አበው በአላህ ባሕሪያት ላይ የሚነሱ የ“እንዴት?” እና ለምን?” ጥያቄዎችን ሁሉ ሲኮንኑ እንደነበሩ መዛግብት ይመሰክራሉ።
› አንድ ግለሰብ በአንድ አጋጣሚ ወደ አል-ኢማም ማሊክ (179 ዓ.ሂ) መጣና የሚከተለውን ቁርኣናዊ አንቀፅ አንብቦ አንድ ጥያቄ አቀረበላቸው፦
ٱلرَّحۡمَٰنُ عَلَى ٱلۡعَرۡشِ ٱسۡتَوَىٰ [طه: ٥]
= «አር-ረሕማን በዐርሹ ላይ ሆነ።» [ጧሃ 5]
“አላህ በዐርሹ ላይ የሆነው እንዴት ነው?” አላቸው! ይህንን ሲሰሙ ፊታቸውን ደፉ፤ ላብም አጠመቃቸው፤ ከዚያም እንዲህ ብለው መለሱ፦
الاِسْتِوَاءُ غَيْرُ مَجْهُولٍ، وَالْكَيْفُ غَيْرُ مَعْقُولٍ، وَالْإِيمَانُ بِهِ وَاجِبٌ، وَالسُّؤَالُ عَنْهُ بِدْعَةٌ.
=› «የአላህ ከዐርሽ በላይ መሆን (“ኢስቲዋእ”) የማይታወቅ አይደለም (ግልፅ ነው)። ‘እንዴት?’ (የሚለው ጥያቄ መልስ) በአዕምሮ የሚደረስበት አይደለም፤ በዚህ (በተጠቀሰው ባህሪ) ማመንም ግዴታ ነው፤ ስለዚህ መጠየቅም ፈጠራ “ቢድዓ” ነው!» ከዚያም (ጠያቂውን)፦ «የቢድዓህ አራማጅ ትመስለኛለህ!» ካሉት በኋላ ከመስጂዱ እንዲወጣ ትዕዛዝ አስተላለፉ!
[አል-በይሀቂይ - “አል-አስማኡ ወስ-ሲፋት” ጥራዝ 2 ገፅ 150-151፣ እንዲሁም “አሊ’ዕቲቃድ” ገፅ 56፣ አድ-ዳሪሚይ - “አር-ረድ-ዱ ዐለ’ል-ጀህሚያህ” ገፅ 33፣ ኢብኑ ዐብዲ’ል-በር - “አት-ተምሂድ” ጥራዝ 7 ገፅ 151፣ አቡ ኑዐይም - “ሒልየቱ’ል-አውሊያእ” ቅፅ 6 ገፅ 325-326፣ አል-ላለካኢይ - “ሸርሑ ኡሱሊ’ዕቲቃዲ አህሊ’ስ-ሱን-ነቲ ወል-ጀማዐህ” ጥራዝ 2 ቅፅ 3 ገፅ 398 ቁጥር 664፣..በሌሎችም በርካታ መዛግብት ሰፍሯል። ይህ በበርካታ ሰነዶች የተረጋገጠ ዘገባ ሲሆን የተለያዩ ሊቃውንት ትክክለኛ ስለመሆኑ መስክረዋል፤ አንድም ታዋቂ ዓሊም በዚህ እውነታ ላይ የሚያጠራጥር ቃል አልተናገረም!]
በተመሳሳይ መልኩ የርሳቸው መምህር የነበሩት አል-ኢማም ረቢዓህ ኢብን አቢ ዐብዲ’ር-ረሕማን (136 ዓ.ሂ) ይህ ጥያቄ ሲቀርብላቸው እንዲህ ብለው ነበር፦
الاِسْتِوَاءُ غَيْرُ مَجْهُولٍ، وَالْكَيْفُ غَيْرُ مَعْقُولٍ، وَمِنَ اللهِ الرِّسَالَةُ، وَعَلَى الرَّسُولِ الْبَلَاغُ، وَعَلَيْنَا التَّسْلِيمُ
«የአላህ ከዐርሽ በላይ መሆን (“ኢስቲዋእ”) የማይታወቅ አይደለም (ግልጽ ነው)። ‘እንዴት?’ (የሚለው ጥያቄ መልስ) በአዕምሮ የሚደረስበት አይደለም፤ መልዕክቱ ከአላህ ዘንድ ነው፤ በመልዕክተኛው ላይ ያለው (ሀላፊነት) ማድረስ ነው፤ በእኛ ላይ ያለው (ግዴታ) መቀበል ነው።»
[አል-በይሀቂይ - “አል-አስማኡ ወስ-ሲፋት” ጥራዝ 2 ገፅ 151፣ አል-ላለካኢይ - “ሸርሑ ኡሱሊ’ዕቲቃዲ አህሊ’ስ-ሱን-ነቲ ወል-ጀማዐህ” ጥራዝ 2 ቅፅ 3 ገፅ 398፣ አል-ዒጅሊ - “ታሪኹ’ሥ-ሢቃት” ገፅ 158 ቁጥር 431፣ አዝ-ዘሀቢይ - “አል-ዑሉዉ ሊል-ዐሊይ-ዪ’ል-ገፍ-ፋር” ገፅ 129 ቁጥር 352]
ይህን ይበልጥ የሚያጎላው ደግሞ ተከታዩ ነጥብ ነው፦
(1-4) መለኮታዊ ርዕሶች በንፅፅራዊ አመክንዮ አይለኩም!
በእምነት ጉዳዮች ላይ ንፅፅራዊ አመክንዮ መጠቀም እንደማይፈቀድ ቀደምት የኢስላም ሊቃውንት ተስማምተዋል።
› ታላቁ የፊቅህ ምሁርና የአቡ ሐኒፋ ቅርብ ተማሪ አል-ኢማም አቡ ዩሱፍ (182 ዓ.ሂ) እንዲህ ብለዋል፦
وَلَيْسَ التَّوْحِيدُ بِالْقِيَاسِ لأَنَّ الْقِياسَ يَكُونُ فِي شَيْءٍ لَهُ شَبَهٌ وَمَثَلٌ، وَاللَّهُ لَا شبه لَهُ وَلا مثل
=› «ተውሒድ በንፅፅራዊ አመክንዮ አይሆንም፤ ምክንያቱም ንፅፅር ቢጤና አምሳያ ላለው ነገር ብቻ የሚሆን ነው። አላህ ደግሞ ቢጤም አምሳያም የለውም!»
[ኢብኑ መንዳህ - “አት-ተውሒድ” ጥራዝ 3፣ ገፅ 306፣ ቁጥር 890፤ አቡ’ል-ቃሲም አት-ተይሚይ - “አል-ሑጅ-ጃህ ፊ በያኒ’ል-መሓጅ-ጃህ” ጥራዝ 2 ገፅ 122]
› እንዲሁም አል-ኢማም አሕመድ (241 ዓ.ሂ) እንዲህ ብለዋል፦
وَلَيْسَ فِي السُّنَّةِ قِيَاسٌ, وَلَا تُضْرَبُ لَهَا الْأَمْثَالُ, وَلَا تُدْرَكُ بِالْعُقُولِ وَلَا الْأَهْوَاءِ, إِنَّمَا هِيَ الِاتِّبَاعُ وَتَرْكُ الْهَوَى
=› «ትክክለኛው ፈለግ ወስጥ ንፅፅራዊ ልኬት የለም፤ ምሳሌም አይበጅለትም! በአእምሮና በግላዊ ዝንባሌ የሚደረስበትም አይደለም! መከተልና ግላዊ ዝንባሌን መተው ብቻ ነው።»
[አል-ላለካኢይ - “ሸርሑ ኡሱሊ’ዕቲቃዲ አህሊ’ስ-ሱን-ናህ..” 1ኛው ጥራዝ፣ ቅፅ 1 ገፅ 156]
› እንዲሁም ታላቁ ሊቅ ኢብኑ ዐብዲ’ል-በር (463 ዓ.ሂ) እንዲህ ይላሉ፦
لَا خِلَافَ بَيْنَ فُقَهَاءِ الْأَمْصَارِ وَسَائِرِ أَهْلِ السُّنَّةِ، وَهُمْ أَهْلُ الْفِقْهِ وَالْحَدِيثِ فِي نَفْيِ الْقِيَاسِ فِي التَّوْحِيدِ
=› «በተውሒድ ጉዳይ ላይ ንፅፅራዊ ልኬት ውድቅ ስለመሆኑ የየከተሞች ሊቃውንት እንዲሁም የፊቅህና የሐዲሥ እውቀት ባለቤት የሆኑት ሌሎች አህሉ’ስ-ሱን-ናዎች መካከል ምንም ውዝግብ የለም!»
[ኢብኑ ዐብዲ’ል-በር - “ጃሚዑ በያኒ’ል-ዒልሚ ወፈድሊሂ” ጥራዝ 2 ገፅ 887]
No comments:
Post a Comment